ለትምህርትም ለኑሮም አገሬን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት፣ አዲስ አበባ ላይ፣ ከጓደኞቼ ጋር የምናስበውንም የምንጭረውንም ነገር የምናስቀምጥበት አንዳንድ ደብተር (Journal) ነበረን። ግጥምም፣ መጣጥፍም፣ ፖለቲካም፣ መዝናኛም … የሆነውን ሁሉ የምንጭርበት ነበር። ነገር ግን ልጫረው እንጂ ለጋዜጣም፣ ለመጽሔትም፣ ለሬዲዮም ሆኖ አያውቅም ነበር። በየወሩ ግድም ባለን የጓደኞች የሥነ ጽሑፍ ጉባዔ እዛው እቤታችን የምናነባቸውን ነገሮች የምናዘጋጅበትም ነበረን። አንድ ቀን ሰብስበን መድበል እናደርጋቸዋለን የሚል ሐሳብ ነበረ። እንዲያውም ኃላፊነቱን ለእህታችን ለጽላት (የዳንኤል ምሽት ይላል የገጠር ሰው) የሰጠናት ይመስለኛል። ከዚያ ኑሮ ሲበታትነን - እኔም አውሮፓዬ ሔድኹ። ዳንኤል ክብረትም፣ አሥራት ከበደም፣ መስፍን ነጋሽም፣ ተስፋዬ ሽብሩም፣ መርሻ አለኸኝም፣ አሉላ ጥላሁንም፣ ያሬድ ገ/መድኅንም፣ ግርማ ወ/ሩፋኤልም፣ ሸዋደግ ሞላም፣ ታምሩ ለጋም፣ ትዕግስት ዳኜም፣ ጽላት ጌታቸውም፣ ምስራቅ ግዛውም ሁሉም ሁሉም በኑሮ ጣጣ ሲጠመድ መድበላችንን ውሃ በላው ወይም መድበላችን ውሃ ጠጣ።
ሲጀመር፦ ወደ ጡመራው ለመዞር ሐሳብ አልነበረኝም። ሥራዬ አብዛኛው ከጽሑፍ ጋር የሚገናኝ እንደመሆኑ ሌላ የጽሑፍ ነገር በመዝናኛነትም ቢሆን መጀመሩ ቀላል ሸክም አይሆንም ብዬ ፈራኹ። የምጽፋቸውንና የምሞነጫጭራቸውን አንዳንድ መጣጥፎች የሚያውቁ ወዳጆቼ “ግዴለም፣ ግዴለም፤ እኮ በል፣ እኮ በል” ብለው ብዙ ጊዜ ሲገፋፉኝ ቆዩ። “እሺ፣ በጄ” አላልኳቸውም።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ወዳጄ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት አዲስ አበባ ከሚታተመው ከ“ሮዝ” መጽሔት ጋር አስተዋወቀኝና “ካልጻፍክ” ሲል ግድ አለኝ። “እንዳልክ” አልኩና መጫጫር ጀመርኩ። ከዳንኤል ጋር ብዙ ዘመን አብረንም ከመኖር፣ አብረንም ከመሥራት ውጥር አርገው ካልያዙኝ እንደማልሠራ ጠባዬን አውቆታል። “ሮዝ መጽሔትም” በየ 15 ቀኑ “ውጥር አድርጎ ሲይዘኝ” በወር ሁለት ነገር መወርወር ያዝኩ። ያንንም እያሰለስኩ በፌስቡክ ላይ ጫንኩት። ዳንኤልን የዛሬ ዓመት አካባቢ “ብሎግ ጀምር፣ ጦምር” ብዬ ግድ ያልኩት እኔ ነበርኩ። አሁን ደግሞ በተራው ዳንኤል ሰሞኑን ወደ ሀገረ አሜሪካ ሲመጣ “መጻፍህ ካልቀረ ብትጦምረው” አለኝ። እኔም “መጻፌ ካልቀረ፣ እስከዛሬስ በየወረቀቱ ላይ ጫጭሬ ያስቀመጥኳቸውንም የምጨምርበት አንዲት “የሕዋው ደብተር ብትኖረኝ ምን ይጎዳኛል” ብዬ "ቁሳቁስ መስጠት ብቻ ሳይሆን መልካም ሐሳብም ማካፈል ጥሩ ነው" በሚል መነሻ ለመጦመር ተነሣኹ።
ዕድሜ ለቴክኖሎጂ፣ ሰው የሚያስበውንና የሚያልመውን፣ የሚፈልገውንና የሚፈቅደውን የሚያስነብብበት፣ የሚያስደምጥበት፣ የሚያሳይበት ሰፊ “አደባባይ” ተፈጥሯል። በፊደል ከሽኖ በጽሑፍ፣ በድምጽ ቀምሮ በምጥን ሬዲዮ (ኦዲዮ) መልክ፣ በቪዲዮ አሳምሮ በዩ-ቲዩብ እና በመሳሰሉት ነገሮች ሐሳቡን ማቅረብ ይችላል። ከሁሉ ከሁሉ ለጊዜው ልቤን የገዛው “ብሎጊንግ” ወይም ጡመራ ነው።
Blogging / ብሎጊንግን “ጡመራ” (መ ሲነበብ ይጠብቃል) ያለው “ደጀ ሰላም” ነው። በሥነ ጽሑፋዊ የመፍጠር ፈቃዱ (“poetic license” እንደሚባለው) “ደጀ ሰላም” የመፍጠር መብቱን ተከትሎ አዲስ ቃል አስተዋውቆናል። “ጦማር” (መ አይጠብቅም) የሚለውን ቃል ወስዶ ግስ አድርጎ፣ ገሰሰውና “መጦመር” የሚል ቃል ፈጥሮ በዚያው አረባው፣ እናም “መጦመሪያ መድረክ”፣ “ጦማሪ” እያለ አስፋፋው። ሌሎቹም ጦማርያን በዚሁ ቃል መጠቀሙን ቀጠሉበት። እኔም በዚሁ እከተላለኹ። እንግዲህ ከማጀቱ ወደ “አደባባይ” ብቅ እንበል። መልካም ንባብ።
No comments:
Post a Comment